በሰሜን አሜሪካ ደቡብ ካሊፎርኒያ በምትገኘው በኦሬንጅ ካውንቲ ውስጥ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን የማቋቋሙ ሀሳብ፣ ደስታና ሀዘንን አብረው የሚካፈሉብት የመረዳጃ ማህበር በነበራቸው 18 የካውንቲው ነዋሪዎች፣ ሐምሌ ፲ ቀን ፪ሺህ፫ (July 17, 2011) ተጠነሰሰ፡፡ ይህንኑ ሀሳብ ከዳር የሚያደርሱ አምስት አባለት ያሉት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተመሠረተ። ከዛም ኮሚቴው ሊቀመንበር፣ ጸሐፊና ገንዘብ ያዥ በመምረጥ ወደ ተግባር የሚያሻግረውን ረጅም ጉዞ “ሀ” ተብሎ ጀመረ።
ኮሚቴው፣ ቤተ ክርስቲያን የማቋቋሙ ስራ ያለ ካህን መከናወን እንደማይቻል በመገንዘብ፣ በወቅቱ የቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የነበሩትን የአባ ፅጌ ድንግል ደገፋውን የአሁኑን የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስን እገዛ ጠየቀ።
በዚሁ መሠረት አቡነ ቴዎፍሎስ ወደ ኦሬንጅ ካውንቲ በመምጣት ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን አመሠራረት ሂደትና ሕግጋት፣ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን ለማቋቋም መሟላት ስላለባቸው መስፈርቶች ለኮሚቴው አባላት በዘርዝር አስረዱ። ኮሚቴው ባቀረበላቸው ጥያቄም፣ በመስከረም ፮ ቀን ፪ሺህ፬ ዓ.ም. (September 17, 2011) ለኦሬንጅ ካውንቲ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ስለ ምሥረታው ሂደት በሰፊው ካስተማሩ በኋላ፣ ዕጣ ተጥሎ የመድኃኔዓለም የፅዋ ማህበር ተመሰረተ።
ለመድኃኔዓለም ምሥረታ ያላሰለሰ ጥረታቸውን የተያያዙት አቡነ ቴዎፍሎስ፣ የኪራይ ቤተ ክርስቲያን አፈላልገው ካገኙ በኋላ፣ ጥር ፳፮ ቀን ፪ሺህ፬ ዓ.ም. (February 4, 2012) የመድኃኔዓለም አገልግሎት በፕላሴንሺያ ከተማ በ451 West Madison Ave ላይ በሚገኘው Holy Cross Melikite ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ሥነ ሥርዓት ተጀመረ።
የፅዋ ማህበሩ፣ ለአመት ከሰባት ወራት ያህል ምዕመናኑን በየወሩ በማሰባሰብ በመንፈሳዊ ህይወት ሲያንጽ ቆይቶ፣ ግንቦት ፳ ቀን ፪ሺህ፭ ዓ.ም. (May 28, 2013) ከቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና አገኘ፡፡ ከዚያም ሚያዚያ ፲፪ ቀን ፪ሺህ፭ ዓ.ም. (April 20, 2013)፣ የቴክሳስ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በተገኙበት ሥነ ሥርዓት፣ የቅዳሴ ቤቱ፣ ቀራንዮ የመድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ተሰየመ። ቀራንዮ የመድኃኔዓለምም፣ በኦሬንጅ ካውንቲ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሆነ። ይህን ተከትሎም፣ በየሁለት ሳምንቱ ቅዳሜ አቡነ ቴዎፍሎስ ከቅድስት ማርያም፣ አባ ላዕከ ከድንግል ማርያም በየተራ በመምጣት መደበኛ አገልግሎት መስጠት ጀመሩ፡፡ በተጨማሪም መምህር ተከስተ አድማሱ፣ ቀሲስ ዮናስ ገብሩ፣ ዲያቆን ዜና ብሉይ፣ ቀሲስ ውድነህ፣ መጋቢ ይሄይስና ዲያቆን ሀይሌ በየተራ እየመጡ አገልግለዋል፡፡
የምዕመናኑን ፍላጎት በበለጠ ለማሟላት በሚል፣ በየሁለት ሳምንት ይሰጥ የነበረው አገልግሎት፣ በየሳምንቱ እንዲሆን ተወስኖ፤ በአባ ሙሴ ገብረሥላሴ አስተዳዳሪነት፤ ከመጋቢት 3, 2007 ዓም (March 12, 2016) አንስቶ ቀራንዮ የመድኃኔዓለም ሳምንታዊ አገልግሎት መሰጠት ተጀመረ። ከዚያም፣ የቤተ ክርስቲያኑ የመተዳደሪያ ደንብ በምዕመናኑ በማጽደቅና የሰበካ ጉባኤ በመምረጥ፣ በተደራጀ መልኩ በመንቀሳቀስ የራሱ የሆነ ቤተ ክርስቲያን እንዲኖረው በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
የቀራንዮ የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን ከምስረታው አንስቶ አሁን ካለበት ደረጃ ለማድረስ፤ የቤተክርስቲያኑ አባቶች፣ ምዕመኑና በተለያዩ ጊዜያት ያገለገሉና በማገልገል ላይ ያሉ የሰበካ ጉባኤ አባላት ከፍተኛውን ድርሻ አበርክተዋል፤ እያበረከቱም ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ድጋፋቸው ላልተለየንን ለሎስ አንጀለስ ለሚገኙት ለድንግል ማርያምና ለቅድስት ማርያም እንዲሁም ለሳንዲየጎው ቅዱስ ገብርኤል ካህናትና ምዕመናን ልባዊ ምስጋና ለማቅረብ እንወዳለን።
ሁሉን ላደረገ ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን፤ ለዘለዓለሙ አሜን።
ወስበሃት ለእግዚአብሔር!
The primary mission and objectives of the Church are as follows:
Unless otherwise stated in these Bylaws, the ensuing words and phrases are defined as follows: