Bapitsm

Baptism

“ያመነ የተጠመቀ ይድናል፡ ያላመነ ግን ይፈረድበታል።” ማርቆስ ፲፮፤ ፲፮
ጥምቀት ማለት በሰዋስዋዊ ትርጉሙ “አጥመቀ፡ አጠመቀ፡ ነከረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የተመሠረተ ቃል ሲሆን በውኃ ውስጥ መጥለቅ ወይም በእላያችን ላይ ወኃ ማፍሰሰ ማለት ነው። ጥምቀት አንድ ምእመን እንደገና ከመንፈስ ቅዱስ ልደት የሚያገኝበት የመጀመሪያ በር ነው። እውነተኛ ጥምቀት የጀመረው ወይም የመሠረተው ጌታችን እየሱስ ነው።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና ተወልዶ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሲሆነው በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ (ሉቃስ ፫፤ ፳፩—፳፫)።

ጥምቀት ማለት በምሥጢራዊ ትርጉሙ ”ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም“ (ዮሐንስ ፫፤ ፭) በሚለው የእግዚአብሔር ቃል መሠረት ከእግዚአብሔር ዳግመኛ መወለድ ማለት ነው። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈሰም የተወለደ መንፈስ ነው ይላል የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት። በመሆኑም ጥምቀት የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ ይባላል።

“ያመነ የተጠመቀ ዘለዓለማዊ ድህነትን ይድናል” የእግዚአብሔር ቃል እንደነገረን አምኖ በመጠመቅ ዘለዓለማዊ ድህነትን ማግኘት ነው። ከዚህ የተነሣ በትምህርተ ሃይማኖት ይህ ክፍል ምሥጢረ ጥምቀት ይባላል።

የልጅነት ጥምቀት፦ የእግዚአብሔር ቃል በሚያዘው መሠረት ካህናት በውኃ ሲጸልዩ በእግዚአብሔር ፍቃድ ውኃው ክርስቶስ በተሰቀለበት ቀን ከጭፍሮቹ አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው ጊዜ ከጎኑ በፈሰሰው ደም በተለወጠው ውኃ ነው።

በመጽሐፈ ኩፍሌ ”በተፈጠራባት ምድር ለአዳም አርባ ቀን ከተፈጸመለት በኃላ ይገዛትም ይጠብቃተም ዘንድ ወደ ገነት አስገባነው። ሚስቱንም በሰማንያ ቀን አስገባናት።“ ይላል። ይህን በመከተል ወንዶች በተወለዱ በአርባ ቀን ሴቶች በተወለዱ በሰማንያ ቀን በጥምቀት አማካይነት ከእግዚአብሔር ተወልደው ገነት መንግሥተ ሰማያት እንዲገቡ ታደርጋለች።

ጥምቀት የማይደገም ነው። ማለት ሁለተኛ ከእግዚአብሔር ለመወለደ አንጠመቅም ለፈውስ ካልሆነ በቀር የቤተ ክርስትያን አባቶች እንዳአስተማሩን “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት” ትርጒሜው ኃጢአትን በምታሰተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን ማለት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጥምቀት ሲያስተምረን “አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት” ይላል ( ኤፌ ፬፦፭)። ጥምቀት የሚፈጸመው ከቅስና ማዕረግ ጀምሮ ወደላይ ባሉት አገልጋዮች ይፈጸማል ማለት ነው ካህን ካልሆነ ግን መፈጸም አይችልም። በማን ሰም እንጠምቃለን? ለሚለው ጥያቄ መልሱ በማቴዎስ (፳፰፥፲፱ — ፳) እንደተጻፈው በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ይደረጋል። የክርስትና አገልግሎት ማለት ወንድ ልጅ በተወለደ በ40 ቀኑ ሴት ልጅ በተወለደች በ80 ቀኗ የሚፈጸም ሲሆን ነገር ግን በዚህ ቀን ያለተፈፀመላቸው ሰዎች አይጠመቁም ማለት አይደለም “የአመነ የተጠመቀ ይድናል” ባለው አምላካዊ ቃሉ በየትኛውም የእድሜ ክልል ለሁሉም ቤተ ክርስትያናችን አገልግሎቱን ትሰጣለች።

በጥምቀት የምናገኘው እግዚአብሔር ስጦታዎች፥

  • ፩፦ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንን የምናገኘው በጥምቀት ነው (ዮሐንስ፫፥ ፫—፭)
  • ፪፦ በጥምቀት አባታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንመስላለን (ገለ ፫፥፳፯)
  • ፫፦ አምነን ስንጠመቅ የመንፈስና የነፍስን ድህንነት እናገኛለን (ኤፌ ፭፥፳፮)
  • ፬፦ የሕይወታችን መሠረቱ በጥምቀት ከእግዚአብሔር ያገኘነው ድኅነት ነው (ማር ፲፮፥፲፮)
  • ፭፦ በጥምቀት ያገኘነው የልጅነት ስጦታ መሆኑን የእግዚአብሔር ቃል ያስተምረናል (ሮሜ ፮፥፩—፲)

When you or your family members are ready to bapitize fill in our Baptism Form and bring it to us. You may download our Baptism Form from here