ሀገራችን ኢትዮጵያ የራሳቸው የዘመን አቆጣጠር ካላቸው ሃገራት አንዷ ስትሆን ይህም የዘመን አቆጣጠር የጥንት ግብጻውያን እንዲሁም ዛሬም ድረስ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የምትጠቀምበት የዘመን አቆጣጠር ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡ ይህም የዘመን አቆጣጠር 13 ወራትን የያዘ ሲሆን 12 ቱ ወራት እኩል ሰላሳ ቀናት ሲኖራቸው የመጨረሻዋ አንድ ወር ግን 5 ቀናት እንዲሁም በአራት ዓመት አንድ ጊዜ 6 ቀናት ይኖሯታል ፡፡ አራቱም ዓመታት በአራቱ ወንጌላውያን ዘመነ ማቴዎስ፣ ዘመነ ማርቆስ፣ ዘመነ ሉቃስ እና ዘመነ ዮሐንስ በመባል የተከፋፈሉ ሲሆን በዘመነ ሉቃስ 13ኛዋ ወር ጷግሜ 6 ትሆናለች፡፡
የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ መስከረም ፩ ወይም (September 11) ይከበራል ይህም ቀን ቅዱስ ዮሐንስ ወይም ዕንቍጣጣሽ ተብሎ ይጠራል።ቅዱስ ዮሐንስ የሚባልበት ምክንያት መጥምቁ ዮሐንስ በሄሮድስ አንቲጳስ ጊዜ ከጳጉሜን ፩ ቀን ጀምሮ ታስሮ ሰንብቶ በመስከረም ፩ ቀን ተቆርጦበት መስከረም ፪ ቀን አንገቱን በሰይፍ ተቆርጦ ስለ ሞተ ሊቃውንት ይህንን በዓል እሱ ራሱ ለኦሪትና ለወንጌል መገናኛ መምህር ስለ ነበረ ይህም በዓል ላለፈው ዘመን መሸኛ፥ ለሚመጣው ዘመን መቀበያ እንዲሆን ብለው በመስከረም ፩ቀን እንዲከበር ስላደረጉ በሱ ስም ቅዱስ ዮሐንስ እየተባለ ይጠራል።እንዲሁም ዕንቁጣጣሽ የተባለበት ምክንያት ንግሥት ሳባ ጥበቡን ሽታ ንጉሡ ሰሎሞንን ለመጎብኘት እየሩሳሌም በሄደችበት ጊዜ የዕንቁ ቀለበት ሰጥቷት ነበርና«ዕንቁ ለጣትሽ» ማለት ነው በሚል እንዲሁም ደግሞ በመስከረም ወር እግዚአብሔር አምላክ ሰማይን በከዋክብት ምድርንም በአበቦች አስጌጣት ወይም አንቈጠቈጣት በማለት ዕንቁጣጣሽ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል ፡፡ አሁን የያዝነው አዲስ ዓመት (2013) ከአራቱ ወንጌላውያን አንዱ በሆነው በማቴዎስ የተሰየመ ዘመነ ማቴዎስ ነው። የጊዜና የዘመን ባለቤት የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር ዘመናችንን ይባርክልን! ወስብሃት ለእግዚአብሔር አሜን!