Wedding

ጋብቻ

“መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን” ዕብራውያን ፲፫፥ ፬
 

ጋብቻን ባርኮና ቀድሶ ለሰው ልጅ የሰጠው እግዚአብሔር ነው። ጋብቻ በአዳምና በሔዋን እንደተጀመረ የታወቀ ነገር ነው። አምላካችን የጋብቻን ጥምረትን የሚመለከተው እንዴት ነው ለሚለው ጥያቄ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዕብራውያን ፲፫፥ ፬ እንዲህ ይላል “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን”። የእግዚአብሔር ቃል ስለ ጋብቻ ሲናገር “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እነደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባቸሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” (ሮሜ ፲፪፥ ፲፪)። በማለት የጋብቻን አንድነት ያስረዳል በመሆኑም ጋብቻ የእግዚአብሔር ፀጋ ነው።

“ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለምና የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት” ብሎ እግዚአብሔር ሔዋንን ከአዳም አካል ፈጠራት (ዘፍ ፪፥፲፰) ። አዳም ከአካሉ የተፈጠረችውን አይቶ እንግዲህ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ሥጋዋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል (ዘፍ ፪፥፲፰) አለ ከዚህ ሰዓትና ቀን አንስቶ ወንድና ሴት አንድ አካል የሚለውን ይዘው ጋብቻ በዚህ ህይወት ውስጥ የሚጓዙበት ትልቅ ትርጉም ያለው ምስጢር ነው።

ጋብቻ በምናስብበት ወቅት በመጀመሪያ ፈቃደ እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ይኖርብናል ከዚያም ከቤተሰብ እንዲሁም ከንስሐ አባት ጋር በመምከር መዘጋጀት ያስፈልጋል ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን “ልጄ ሆይ የአባትህን ምክር ስማ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው ለራስህ የሞገሰ ዘውድ ለአንገትህም ድሪ ይሆንልሀል” (ምሳሌ ፩፥፰—፱) ። ጋብቻ ክቡር እንዲሆን የትዳር ጓደኛሞች እርስ በርሳቸው መከባበር አለባቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ይህን ይናገራል (ሮሜ ፲፪፥፲—፲፬) “እናም ባልና ሚስት በጋብቻ ከተጣመሩ በኋላ እንደ ቃሉ በመከባበር መኖር አለባቸው”።

ጋብቻ በጣም ሰፋ ያለ ቃል ያለው ሲሆን ከዚህ በመቀጠል ዋና ዋናዎችን አላማዎች እናያለን፦

  • ከጋብቻ አላማዎች አንዱ መረዳዳት ነው፤ መረዳዳት ማለትም በሥጋ ብቻ አይደለም በነፍስም ጭምር ነው። ለሥጋቸው በሥራ ሲረዳዱ ለነፍሳቸው ደግሞ በጸሎት ይረዳዳሉ።

  • ሌላው የጋብቻ አላማ ዘር መተካት ነው ፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው እግዚአብሔር ባረካቸው እንዲሁም አላቸው ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙልዋት፥ (ዘፍ ፩፥፳፰) ። ይህ ሲባል ግን ዘር ሲተካ በእግዚአብሔር ፍቃድ የሚኖሩ መሆን አለባቸው።

የተከበራችሁ ምዕመናን ይህንን ሥርዓት ለማከናወን በሥርዓተ ቤተክርስቲያን ጋብቻ ለመፈጸም እንዲያበቃን በጾም በጸሎት አምላካችንን መጠየቅ አለብን። እንዲሁም ከተጋባን በኋላ ሥጋወደሙ ለመቀበል ወደ ቤተ ክርስትያን መምጣት ያለብን ከትዳር አጋራችን ጋር መሆን አለበት።

ስለዚህ ጋብቻ ለምትፈጹሙ ሁሉ ቤት ክርስቲያናችን አገልግሎቱን ለመስጠት በርዋ ሁል ጊዜ ክፍት መሆኑ በእግዚአብሔር ስም ልናሳስባችሁ እንወዳለን።